ጌታዬ አላህ ነው
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦ {እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።} [አል በቀራ፡ 21]
- ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦ {እርሱ አላህ ነው፤ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ።} [አል ሐሽር፡ 22]
- ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦ {የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱ ሰሚ ተመልካች ነው።} [አሽ ሹራ፡ 11]
- አላህ የእኔም ጌታየ የሁሉ ነገርም ጌታው ነው፤ የሁሉም ንጉስ (ባለቤት) ፣ የሁሉም ፈጣሪ ፣ የሁሉም ሲሳይ ለጋሽ እና የሁሉ ነገርም አስተናባሪ ነው።
- አምልኮ (ዒባዳ) በብቸኝነት የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፤ ከእርሱም ውጭ ሌላ ጌታ የለም፤ ከእርሱም ውጪ ሌላ እውነተኛ አምላክ የለም።
- አላህ ለራሱ ያፀደቀውና ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ለአላህ ያፀደቋቸው እጅግ ውብ የሆኑ ስሞች እና ምሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት። እነዚህም የሙሉነት (የፍጹምነት) እና የውበት ጫፍ የደረሱ ናቸው። እርሱን የሚመስለው ምንም የለም፤ እርሱ ሰሚ ተመልካችም ነው።
ከአላህ እጅግ ውብ የሆኑ ስሞች መካከል፦
- አር-ረዛቅ (ሲሳይን ሰጪ/ለጋሽ)
- አር-ረሕማን (እጅግ በጣም አዛኝ)
- አል-ቀዲር (ሁሉን ቻይ የሆነ)
- አል-መሊክ (የሁሉም ንጉስ)
- አስ-ሰሚዕ (ሁሉን ሰሚ)
- አስ-ሰላም (ከእንከን ሁሉ ነፃ የሆነ ፍፁም፤ የሰላም ባለቤት)
- አል-በሲር (ሁሉን ተመልካች)
- አል-ወኪል (አስተዳዳሪው፣ የሁሉም ጉዳይ ባለቤት፤ የፍጡሩ ሁሉ ተወካይ)
- አል-ኻሊቅ (የሁሉም ፈጣሪ)
- አል-ለጢፍ ( ውስጥ ዓዋቂ)
- አልካፊ (ለሁሉም የሚበቃ)
- አል-ገፉር (መሃሪ)
* አንድ ሙስሊም የአላህን ድንቅ ፍጥረታት እና ነገራቶችንም ለባሮቹ እንዴት እንዳገራቸው ያሰላስላል። ሁሉም ፍጡራን ታዳጊዎቻቸው አድገው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ የዚህ አንዱ መገለጫ ነው። ፈጥሮ ለሚራራላቸው አምላክ ጥራት ተገባው። ከርህሩህነቱ መገለጫዎች መካከል ሙሉ በሙሉ (ሓቁን መወጣት የማይችሉ) ደካማ ከመሆናቸውም ጋር እነርሱን የሚረዳ እና ሁኔታቸውንም የሚያስተካክል መሆኑ ተጠቃሽ ነው።